የፕሬዝዳንቷ መልዕክት

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ባለፉት ዓመታት ልማትን፣ የፆታ እኩልነትን፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ለማራመድ ያለመታከት ሲሠራ ቆይቷል። ምንም እንኳን በተቀዳጀናቸው ስኬቶች የምንኰራ ቢሆንም ሴቶች ሙሉ ተሳትፎን የሚያረጋግጡበት፣ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ራዕያችንን ለማጎናፀፍ በርካታ
ተግባራት እንደሚቀሩን መገንዘብ አለብን። ፅኑ እምነታችን የተመሰረተውም ለሴቶች የእኩልነት መብቶች ዋስትና በሚሰጠው ሕገመንግሥታችን ላይ ነው።
የሚከተለው ስትራቴጂያዊ እቅድ ፌዴሬሽኑ ከራሱ ነባራዊ ሁኔታ እና መንግሥት የፌዴሬሽኑን ዓላማዎች ለመደገፍ ያመነጫቸውን ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች በመለየት ያቀርባል። ባሁኑ ወቅት ሁሉም የመንግሥት ዘርፎች ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮችና እነዚህን ለመወጣት የሚያስችሉ ጣልቃ ገብነቶችን በቅጡ በተሰናሰለና ተከታታይነት ባለው መልኩ ያካተቱ ፖሊሲዎች አሏቸው፡፡ ስትራቴጂያዊው እቅድ እነኚህን በመመሪያነትና ድጋፍ ይጠቀምባቸዋል። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ራዕይ ኢትዮጵያን በህዝቦቿ ተሳትፎና ነፃ ፍላጎት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣
መልካም አስተዳደርና ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት እንድትሆንና አንዴ ከድህነት ከተላቀቀችም በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጎን እንድትሰለፍ ነው። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የሴቶችን ጥቅሞች ለማሳደግ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር ይተባበራል፤ ይቀናጃል።ፌዴሬሽኑ በተጨማሪም ባለፉት ሁለት አሠርት አመታት በኢትዮጵያ ሴቶች ህይወት ውስጥ በተፈጠረው አዎንታዊ ለውጥ ላይ በመመስረት ለበለጠ ውጤታማነት ይሠራል፡፡ ለአብነት፣ የጤና ኤክስቴሽን ፓኬጁ የሞትን መጠን ቀንሷል፤ እንዲሁም የሴቶችንና የህፃናትን ህይወት አሻሽሏል፡፡ በተመሳሳይ የትምህርት ፓኬጁ ሴቶች ለትምህርትና ሥልጠና ያላቸውን ተደራሽነት አሳድጓል፡፡ በገጠር የሚኖሩ በግብርና ፓኬጁ የተሳተፉ ሴቶች ምርታማነት ሲያድግ የሥራ ጫና ቀንሶላቸዋል፡፡ እነኚህና ሌሎችም በመንግሥት የተወሰዱ ተነሳሽነቶች ለስትራቴጂያዊ ራዕያችን መሠረቶች ናቸው፡፡ እነዚህን በማስፈፀም ሂደት ያጋጠሙ ተግዳራቶችን ደግሞ ለመቅረፍ
የተደረገው የእስካሁን ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡